ResearchTargeted Threats

የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች በአዲስ የስለላ ሶፍትዌር ጥቃት ዒላማ ስር

ጸሐፍት – ቢል ማርክዛክ፣ ጂኦፍሪ አሌክዛንደር፣ ሳራ ማኩን፣ ጆን ስኮት-ሬይልተን፣ ሮን ዲበርት

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች የአዶቤ ፍላሽ ማሻሻያና የፒዲኤፍ ፕለግኢን በማስመሰል የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌር በያዙ ኢሜይሎች ዒላማ እንደተደረጉ የሚገልጽ ሪፖርት የሲትዝን ላብ ይፋ አድርጓል፡፡ ዒላማ ከተደረጉት መሀል መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ያደረገ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ብዙኃን መገናኛ፣ የኦሮምያ ሚድያ ኔትወርክ (OMN)፣ አንድ የፒኤችዲ ተማሪና አንድ የህግ ጠበቃ ይገኙበታል፡፡

ከተከታተልናቸው ጥቃቶች እንደተመለከትነው የስለላ ሶፍትዌር ጥቃት የደረሰባቸው አካላት ትክክለኛውን የeastafro.com ቪድዮ ፖርታል የሚመስል eastafro[.]net ወደሚባል አደገኛ ድረገጽ የሚያገናኝ ሊንክ በኢሜይል ይደርሳቸዋል፡፡ ይህ ኢሜይል የተላከለት ግለሰብ ሊንኩን ሲጫን ቪድዮውን ከመመልከቱ በፊት የአዶቤ ፍላሽ ማሻሻያና የፒዲኤፍ ፕለግኢን እንዲጭን ይጠየቃል፡፡ ምርመራችን የስለላ ሶፍትዌሩ (ስፓይዌሩ) መነሻ በስለላ ሶፍትዌር ሽያጭ ንግድ ዘርፍ ላይ አዲስ መጤ ወደሆነው የእስራኤል ሳይበርቢት መርቶናል፡፡ ሳይበርቢት በኤልቢት ሲስተምስ (Elbit Systems) ሙሉ ባለቤትነት የሚመራ የቅርንጫፍ ድርጅት ነው፡፡ የስለላ ሶፍትዌሩ በቅርቡ ስያሜውን PC 360 በማለት የቀየረውን የፒሲ ስለላ ሲስተም (PC Surveillance System (PSS)) ምርት ይመስላል፡፡

በeastafro[.]net የሚታየው የሐሰት ፍላሽ ፕሌየር ማሻሻያ መልዕክት

 

የስለላ ሶፍትዌሩ ሰርቨር የሶፍትዌሩን አንቀሳቃሽና የተጠቂውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ግልጽ የምዝግብ ፋይል (public logfile) እንዳለው አይተናል፡፡ ይህም የአጥቂዎችንና የተጠቂዎችን ማንነት እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ የሶፍትዌሩ አንቀሳቃሾች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙና ከተጠቂዎች መሀል የተለያዩ የኤርትራ ድርጅቶችና የመንግስት ወኪሎች እንደሚገኙበት ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪም እንደ ናይጄሪያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሩዋንዳ፣ ኡዝቤኪስታንና ዛምቢያን በመሳሰሉ አምባገነናዊ አዝማሚያ ያላቸው መሪዎች በሚገኙባቸው አገራት የስለላ ሶፍትዌሩ በግልጽ ሥራ ላይ እንደሚውል ምርመራችን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎችም ላይ ያለአግባብ ስለሚጠቀመው የስለላ ሶፍትዌር ማስረጃ (የሀኪንግ ቲም አርሲኤስ እና የጋማ ግሩፕ ፊንስፓይን ጨምሮ) እ.አ.አ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሲትዚን ላብ ቀደምት ጥናት፣ የሚድያ ዘገባዎችና እንዲሁም በአሜሪካ ፌዴራል ፍርድቤቶች በተመሠረተ ክስ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የስለላ ሶፍትዌርን ያለአግባብ መጠቀም የሚያስከትለው ውጤት ያን ያህል ባይሆንም የስለላ ሶፍትዌር አምራች ንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለኢትዮጵያ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህ ሪፖርት በግልጽ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ፖለቲካን የተመሠረተ የዲጂታል ስለላ እንደቀጠለ ነው፡፡

ህጋዊ መንገድን የተከተለ የምርመራ ዘዴና መሣሪያዎች ጥቅም ቢኖራቸውም ያስተዋልናቸው ጉልህ የሆኑ ስጋቶችና ህገወጥ ስለላ ችላ ሊባሉ አይገባም፡፡ መንግስት ህጉን እንዳይተላለፍ የሚረዱ ጠንካራ መቆጣጠሪያዎች በሌሉበት እንዲሁም የስለላ ሶፍትዌር አምራች ድርጅቶች የሚመሩበት ጠንካራ ደንብ በሌለበት፤ አምባገነናዊ መሪዎች ተጠያቂ የሚያደርጓቸውን ግለሰቦችንና ተቋሞችን መሰለልና ማደናቀፍ እንደሚቀጥሉበት እናምናለን፡፡

ሙሉ ሪፖርቱን በኢንግሊዝኛ ለማንበብ ይህን ይጫኑ፡፡

የዚህን ጥናት ሕጋዊ እንድምታ ትንታኔ በኢንግሊዝኛ ለማንበብ ይህን ይጫኑ፡፡

የሲትዚን ላብ ዳይሬክተር ሮን ዲበርት ስለዚህ ጥናት የጻፈውን ብሎግ ፖስት በኢንግሊዝኛ ለማንበብ ይህን ይጫኑ፡፡

የሲትዚን ላብ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ጥናት በኢንግሊዝኛ ለማንበብ ይህን ይጫኑ፡፡

Note on Translation: This is an informal translation of the original report in English. This informal translation may contain inaccuracies. It is intended only to provide a basic understanding of our research. In the event of a discrepancy or ambiguity, the English version of this report prevails.